!

ልቅ ምዕራፍ : - ክፍል አንድ

ከሥርጉተ ሥላሴ - ግንቦት 2000 ዓ.ም.

 

በመከራው ሁሉ ተደስቶ የኖረው የብፁእ የቅዱስ ጳውሎስ መልዕክት ወደ ሮሜ ሰዎች ምዕ 7 ቁ. 11 “ ... ኃጢያት ምክንያት አግኝቶ በትዕዛዝ አታሎኛልና በእርስዋም ገድሎኛል:: ... “ ቁ. 19 “የማልወደውን ክፉን ነገር አደርጋለሁ :: የማልወደውን የማደርግ ከሆንኩ ግን ያን የማደርገው አሁን እኔ አይደለሁም:: በእኔ የሚኖር ኃጢያት ነው እንጂ ...“ የጥያቄ ምልክት:: ማዕዘናዊ ዕይታ ፣የተንጠለጠለ ተስፋ፣ ኮረብታማ፣ ደልዳላ ፣ ድልድል:: እንደገና  ቁልቁለት፣ ልቅ::

  

  ደግሞ አቀበት ፣ መቃተት፣ በምጥ መዋጥ :: የጥያቄ ምልክት:: ሠርዶ መሳይ ሰንበሌጥ ልምሰል ያለ የውሸት ቅብ:: ለበጣ:: የእበት ልቅልቅ ዓይነት በቃ እንደነገሩ:: ሲጥ ሲጥ :: ሲጥጥ - ሲጥጥ :: አርባውን አስቀድሞ ያወጣ፣ በቁሙ ተስካር ያበላ:: በሞትና በሕይወት መካከል ያለ ደመ ነፍሱን የተገተረ የዛሬ 300 ዓመት ሊያልፍም የሚችል የአሽዋ ድርድር :: ገና ከሩቅ ሲያዩት ያኮረፈ ቃሬዛ ላይ ያለ፣ ለኑዛዜ የተሰናዳ ህንጣ :: አስታማሚ ሳይፈልግ ታማሚ፣ መድኀኒት የማይሻው በሽተኛ ህንጣ፣ ከፊት ለፊቱ ካለው አንድ የምግብ የዕቃ መደበር ሜግሮ ላይ ሆኜ ተመለከትኩት እንደ ከፋው ነው:: በስተጀርባው ሆኜም ከ605 አውቶብስ መናኸሪያ ቆም ብዬም አየሁት::በደረቱ ላይ ሁሌ በሚፈሱት እንባዎቹ ጠቁሯል:: አረንጓዴ ገላዎቹን ክፉኛ አበልዞታል:: በዚህም ክፉኛ አዝነዋል:: አስተዛዛኝም ሆነ ምሾ ደርዳሪ ግን አላሰኘውም::

 

   እንደገናም በሁለቱ ጎኖቹ ያሉትን የመተንፈሻ ቧንቧዎቹንም ጥቂት ጠጋ ብዬ ተመለከትኳቸው:: ተፈርዶባቸዋል:: ውሀ ሲሄድባቸው የከረሙ ዓለቶች መስለዋል:: ለዘር ለብጣሽ ለዛ የሚባል ነገር አልፈጠረለትም:: ታሬና ቁንጮው ሻግቷል:: ሸጋታው  ራሱ መከራን ይጠራል እንጂ ደስታን አይፈጥርም::የሀዘን ሲቃን ያቃብጣል እንጂ ተስፋን ፈጽሞ አይቸርም::የደረቀ ተስፋ መናኸርያ::እኔም እንደ እሱ ደመ ነፍስ ሆኜ አለሁ:: በሱ ልከዘን ተፈርዶብኛልና :: ወደ ውስጥ ዘለቅሁ:: እግሮቼ የእኔ አልመሰሉኝም:: ከብደውኛል:: አዘቅዝቄ ተመለከትኳቸው:: እረ በዕይታ ቀመራዊ ሂደት እኔ ላለሁበት ያትውልድ ፈንገጥ ብዬ እንደምኖር እሱ እራሱ ለክፍት ጫማ የተፈጠሩት ውብ ተረከዞቼ ከነ መሀባቸው መሆናቸውን አረጋገጥኩ::

 

   ... ግን ወደ አይቀሬው አፍ ወዳለው መቃብር ቤት ገሠገስኩ ክብድ አለኝ:: ፍራው/ ወይዘሮ ሹቱደር ማርጋሪን የስደተኛው ካምፕ ኃላፊ ክፍሌን ከፈቱልኝ:: በእውነት አያስገባም እምል - የእምል ድልብ ተሽቀዳድሜ ብለቅ ጥሩ አድርጎ ያስታመማቸውን ሁለት ባለ እንጨት መስኮቶች ከፈትኳቸው:: እንደ ነገሩ ናቸው::  ፈቃድ ተሰጠኝ ወይም መቆም ወይ መቀመጥ:: የቁም እስር አይነት መላወሻ የላትም ክፍሏ:: ጣሪያ ግድግዳውን ተመለከትኩት:: ውር ውር የሚሉ ጉዶች አሉበት:: ገለጥ አድርጌ አየኋቸው:: እንዴት ነሽ ለማለት ይሆን ? ደነሱብኝ::  በተገነጠለው የግድግዳ ካርቶን ውስጥ ገለጥ አድርጌ ተመለከትኩት:: በመቶ የሚቆጠሩ የበረሮ ክምችቶች የሠርግና የምላሽ ቀናቸው ነበር:: ባለ ቬሎ ... ባለ ክሬም  ...

   

   ኃይለኛ ወጀብ አዘል ዝናብ ያን በምርኩዝ ተንገዳግዶ የቆመውን መስኮት ገፍትሮ በጥፊ አጮለኝ:: እንጨቶቹ ድንኳን ተጥሎላቸዋል:: ሳልስት ላይ ተቀምጠዋል:: ወይ አንተ ወይ እኛ ግን መቼ ይባባላሉ:: ከዚያ ጉደኛ ወጀብ ጋር የጥያቄ ምልክት በመስመርና በስንጥቅ፣ በስንጥርና በፍንጭት ሽርሽሩ ቀለጠ:: በመላጣ ተስፋ ወጣ ገባ፣ ገባ ወጣ ጨዋታ:: ሻታ ይዞራል ታካች የጥያቄ ምልከት:: ከባህር ወላል ታችና ላይ፤ ላይና ታች የጠቆረ ጥቃቅን ድሪቶአማ ቅዝቃዜ ሩሄን ፋታ ነሳት::

    መከራ የገረፈው መስታወትም ፊት ለፊቴ ተገትሯል:: ጠንጋራ! ነገ ሌላ ቀን ነው በማለት ቀጣዩን ዘመን ካሳለፍኩት ጨጎጎታማ ዘመን ጋር እንዳመሳክርለት አቤቱታውን አቀረበ:: ሱባኤው ከአንተ ጋር ብገባ ይሻል ይሆን የጥያቄ ምልክት! ድህና በሚባልለት ጥቂት አካሉ ላይ ተግትሬ ራሴን አየሁት:: በኢማጅኔሽን የማልኖር፣ የራሴ ምንገድ ያለኝ ራሴን መርምሬ የተገነዘብኩ ፍላጎቴን የማውቅ እውነት ፈላጊ ቋሚ ባህርይ ያለኝ፣ በአርቲፊሻል የትናንት የዛሬ ምን አልባትም አርጅቶ በሚመጣው የነገ ገጠመኝ ራሴን ሸንግዬ መኖር የማልችል በ አስተሳሰብ፣ በጉዞ  በሀዘን እና በምሬት የማረተው መስታወቴ አሳምሮ ነገረኝ:: አዎ በጭላጭል የነበረችው ትንሽ ብጣቂ ሻማ አንቀላፋች ግን ለምን የጥያቄ ምልክት::

 

ይቀጥላ . . .

 

Back to maedot<< Back to Menu        write your Comments